ታላቅ የተቃውሞ ሰልፍ ጥሪ!
በአውሮፓ ለምትገኙ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ
የአፋር የሰብአዊ መብቶች ድርጅት፣ የኢትዮጵያዊያን ኮሚውኒቲ በቤልጂየም እና የሉቅማን የኢትዮጵያዊያን-ቤልጂማዊያን ሙስሊሞች ማህበር በጥምረት ጥሪያችንን እናቀርባለን፤
ሰልፉ የሚካሄድበት ቀንና ሰአት፦ ሜይ 16፣ 2012 ከ13፡00 ሰዓት ጀምሮ
ሰልፉ የሚካሄድበት ቦታ፦ በብራስልስ አውሮፓ ካውንስል ፊት ለፊት
በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ ከዕለት ወደ ዕለት አስከፊ ወደ ሆነ ደረጃ ላይ እየደረሰ ይገኛል። በግለሰቦች ላይ ከሚደርሰው የመሰወር፣ የጅምላ እስራት፣ በድብደባ ማሰቃየት፣ አፈና እና ግድያ፣ ከስራ መባረር፣ ንብረት መነጠቅ እና ሌሎች በደሎች…በተጨማሪ የተወሰኑ የሕብረተሰብ ክፍሎችን፣ የኃይማኖት ተቋማትን፣ የሙያና የሲቪክ ማኅበራትን፣ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶችን እና የፖለቲካ ፓሪቲዎችን ዒላማ ያደረገ የጥቃት እርምጃ በተደጋጋሚ በመንግስት በኩል እየተወሰደ ይገኛል። እነዚህ የመብት ጥሰቶች መፍትሄ ሳይበጅላቸው ለረዥም ዘመናት ከቆዩት የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማሕበራዊ ቀውሶች ጋር ተዳምሮ አገሪቱን እጅግ አስፈሪ ወደሆነ ሁኔታ እያመራት ይገኛል። ነገሮች ሙሉ በሙሉ ከመንግስት ቁጥጥር ስር ወጥተው አገሪቱ ማቆሚያ ወደ ሌለው ቀውስና እልቂት ውስጥ ከመግቧቷ በፊት የአለም አቀፉ ማኅበረሰቡ ተገቢውን ጫና በመንግስት ላይ ያደርግ ዘንድ ለማሳሰብ ይህን የተቃውሞ ሰልፍ አዘጋጅተናል። በዚህም መሰረት ለአለም አቀፉ ማኅበረሰቡ የምናቀርባቸው ነጥቦች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል።
መንግስት የተለያዩ ሰበቦችን በመፍጠር በአገሪቱ የተለያዩ ማጎሪያ ቤቶች ያሰራቸውን የፖለቲካ እስረኞች ባፋጣኝ እንዲፈታ፤
መንግስት ሽብርተኝነትን ለመዋጋት በሚል ሰበብ በሃሰት በአሸባሪነት ወንጅሎ ያሰራቸውን ጋዜጠኞች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላትን ባስቸኳይ እንዲፈታ፤
በአፋር ፣ በደቡብ፣ በጋምቤላ እና በኒሻንጉል ክልል ውስጥ ልማትን ለማስፋፋት በሚል ሽፋን ዜጎችን ከመኖሪያ ቀያቸው የማፈናቀል እርምጃ ባፋጣኝ እንዲቆም፤ የመንግስትን ሕገ ወጥ እርምጃ በመቃወማቸው የተነሳ ለእስር የተዳረጉ አርሶ አደሮች እና ሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች ባፋጣኝ እንዲፈቱ፤
መንግስት በኃይማኖት ተቋማት ውስጥ ጣልቃ በመግባት እያደረገ ያለውን ሕገ ወጥ ተግባር ባፋጣኝ እንዲያቆም፤ በተለይም በእስልምና እምነት ተከታዮች ላይ እየደረሰ ያለው ወከባ፣ ጫና እና ጣልቃ ገብነት ግዲያና ዛቻ እንዲቆም፤ በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ገዳማትና ታሪካዊ ስፍራዎች ላይ እየደረሰ ያለው ውድመት እንዲገታ፤
ሕጋዊ በሆነ መንገድ የመብት ጥያቄዎችን በማንሳታቸው ብቻ ከሥራ ገበታቸው የተባረሩ መምህራ ባፋጣኝ ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ፤ እንዲሁም መንግስት የመምህራኑን አስተዳደራዊ ጥያቄዎች ከማፈን ተቆጥቦ ተገቢዎን ምላሽ እንዲሰጥ፤
በኢትዮጵያ በነጻነት የመደራጀት፣ የመሰብሰብ፣ ሃሳብን የመግለጽ፣ መንግስትን በሰላማዊ ሰልፍ የመቃወም እና ሌሎች መሰረታዊ መብቶች ላይ የሚደረገው ከፍተኛ አፈና እና ጫና እንዲቆም እንጠይቃለን።
ለበለጠ መረጃ በስልክ ቁጥር +32 477 327 090፤ +32 486 454 955፤ +32 486 336 367 ሊደውሉ ይችላሉ::
የኃይማኖት፣ የዘር፣ የቋንቋ እና የፖለቲካ አመለካከት ልዩነቶቻችን የኢትዮጵያዊነታችን ውበት እና የአንድነታችን መገለጫዎች ናቸው!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
አስተባባር ኮሚቴው!!



















Recent Comments