ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች አብደዋልን?

ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች አብደዋልን?

By Nasrudin Ousman

‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ኢስላማዊ መንግሥት የመመሥረት ዓላማ አንግቦ የሚንቀሳቀስ ቡድን አለ››የሚለው አባባል ለእኔ ትርጉም አልባ ነው፡፡ እውነት ነው ብዬ ለመቀበልም በጣም ይቸግረኛል፡፡ ይህን ከመሰለ የፈጠራ ወሬ የሚገኘው ፖለቲካዊ ትርፍ ምን እንደሆነም ፈጽሞ አልገባህ ብሎኛል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ኢስላማዊ መንግሥት ለመመሥረት የሚንቀሳቀስ ቡድን ካለ፣ ያንን ቡድን ከማንም በላይ እና በፊት አምርሮ የሚቃወም እና የሚያወግዘው ኢትዮጵያዊው ሙስሊም ነው፡፡

ዶ/ር ጀይላን ለአል ጀዚራ ቴሌቪዥን በአረብኛ ሲናገሩ፣ ‹‹የበርካታ ሃይማኖት ተከታዮች በሚገኙባት ኢትዮጵያን የመሰለች አገር ኢስላማዊ መንግሥትን ስለመመሥረት ማሰብ እብደት ነው››ብለዋል፡፡ እኔን ጨምሮ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ሙስሊም ይህን አባባል በእጅጉ እንጋራለን፡፡…በ1960ዎቹ አጋማሽ ‹‹የሃይማኖት እኩልነት ይከበር!››እያሉ በታላቅ ሕዝባዊ ሰልፍ የጮሁት ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች፣ በዘመነ ኢሕአዴግ፣ በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት ‹‹መንግሥት እና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው፤ መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፤ ሃይማኖትም በመንግሥት ሥራ ላይ ጣልቃ አይገባም››ተብሎ በይፋ ሲደነገግ ከማንም በላይ ጮቤ የረገጡ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች፣ ዛሬ በዚህችው ኢትዮጵያ ኢስላማዊ መንግሥት የመመሥረት ዓላማ አንግበው ሊንቀሳቀሱ አይከጅሉም በእርግጥም ካላበዱ በስተቀር፡፡ አላበድንም! እደግመዋለሁኝ አላበድንም!!

ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በአገራችን ኢትዮጵያ፣ እኛ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችን ክፉኛ ያስቆጣ፣ ክፉኛም ግራ ያጋባ አንድ ትልቅ ችግር ተፈጥሯል፡፡ በአሁኑ ሰአት ከችግሩ ጋር በቀጥታ እየተጋፈጥን ያለነው እኛው ሙስሊሞቹ ብቻ ብንሆንም ቅሉ፣ ችግሩ ግን ቆም ብሎ በሰከነ አዕምሮ የሚያስብ ማንኛውንም ኢትዮጵያዊ ዜጋ የሚመለከት፣ ሙስሊሙን ኅብረተሰብ ብቻ ሳይሆን እርሱንም ሊያስቆጣ የሚችል ወይም የሚገባው ነው ብለን እናምናለን፡፡ …ሙስሊም ያልሆነው ኢትዮጵያዊ ወገናችን የችግሩን ጥልቀት እና ክብደት ይረዳ ዘንድ ራሱን አንድ ጥያቄ ብቻ እንዲጠይቅ እንፈልጋለን ‹‹እንዲህ ዓይነት ነገር በእኔ ላይ ቢፈፀም ኖሮ አሜን ብዬ እቀበላለሁኝን?››…


እኮ እንዴት ያለ ነገር?

ችግሩ በሙስሊሞች የተፈጠረም አይደለም፡፡ በሙስሊሞች መካከል የተፈጠረም አይደለም፡፡ እውነቱን በገደምዳሜ ሳይሆን በግልጽ ለመናገር ችግሩ የተፈጠረው በመንግሥት እና በመንግሥት አማካይነት ብቻ ነው፡፡ በጥቅሉ ሲነገር፣ የችግሩ መሠረታዊ መነሾ የኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ለማመን በሚያዳግት ድፍረት (incredible boldness) በሃይማኖት ጉዳይ ውስጥ ‹ጭው ብሎ መግባት›ነው፡፡ ‹ጭው ብሎ መግባት›የሚለውን አገላለጽ የተጠቀምሁት፣ መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ መግባቱ አዲስ ስላልሆነ ነው፡፡ በሌሎች ሃይማኖቶች አኳያ ለመናገር ለጊዜው በቂ መረጃ ባይኖረኝም፣ ሙስሊሙን በተመለከተ ግን ቢያንስ ከ1987 ወዲህ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት ከኢሕአዴግ ቁጥጥር ውጪ ሆኖ አያውቅም፡፡ የጣልቃ አገባቡን ደረጃና መልክ ስናይ ግን የአሁኑ (በጥቅሉ ከ2000፣ በይፋ ደግሞ ከሐምሌ 2003 ወዲህ ያለው) እና የከዚህ ቀደሙ (ከ1987 –2000) የሰማይና የምድር ያህል የተራራቁ ናቸው፡፡ ጣልቃ አገባቡ እንዳሁኑ ፍፁም ጀብደኝነት የተመላበት ሆኖ አያውቅም፡፡

እንዳልሁት ላለፉት 17 ዓመታት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት ከመንግሥት ቁጥጥር ውጭ ሆኖ አያውቅም፡፡ ሙስሊሙ ኅብረተሰብም አንድያ የሃይማኖት ተቋሙ ከፖለቲካ መሣርያነት ባለፈ የማኅበረሰቡን መንፈሳዊ ህይወት ለማበልፀግ የረባ ሥራ አለመሥራቱ ሲያሳዝነው ቆይቷል፡፡ እንዲያም ሆኖ ቢያንስ በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት የተረጋገጡ መብቶቹን በመጠቀም እምነቱን በነፃነት ለማራመድ፣ ለመተግበር እና ለማስተማር የሚያደርገው የግል እና የወል ጥረት ስላልተስተጓጎለበት ከተቋሙ ብዙም ሳይጠብቅ በሰላም ኑሯል፡፡

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን የኢሕአዴግ መንግሥት አንዳችም የሙስሊሙን ማኅበረሰብ ይሁንታ እና እውቅና ሳይጠይቅ፣ በዚሁ እርሱ በሚቆጣጠረው ‹‹የሙስሊሙ ማኅበረሰብ ተቋም››ላይ የ‹‹አሕባሽ››አስተምህሮ አራማጆችን በመሾም፣ ይህንኑ አስተምህሮ በ‹አሕባሻዊው›ጠቅላይ ም/ቤት አስፈፃሚነት፣ በኢትዮጵያ ሙስሊም ኅብረተሰብ ውስጥ ለማስረፅ (ለመጫን ወይም ለማስጫን) በትጋት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ በሚሊዮኖች የምንቆጠረውን ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በአሕባሽ አስተምህሮ የማጥመቅ ‹‹ተልዕኮ እና ሥልጣን››የተሰጠው ‹‹አሕባሻዊው ጠቅላይ ም/ቤት››ተልዕኮውን የሚፈጽመው የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር በሚያደርግለት ቀጥተኛ ድጋፍ እና የቅርብ ክትትል ነው፡፡

መንግሥት በሙስሊሙ ኅብረተሰብ ተቋም ላይ የ‹አሕባሽ›አስተምህሮ አራማጆችን የሾመው በ2000 ቢሆንም፣ ም/ቤቱ በአሕባሽ አስተምህሮ የማጥመቅ ዘመቻውን በይፋ የጀመረው በሐምሌ ወር 2003 ሐሮማያ ላይ ባካሄደው የመጀመርያ የሥልጠና ጉባዔ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሙስሊም ኅብረተሰብ ‹‹እንዴ! ምን እየተሠራ ነው?!››ብሎ ማጉረምረም የጀመረውም ያኔ ነው፡፡ [በነገራችን ላይ ያንን ‹‹ታሪካዊ››የሥልጠና ጉባዔ በንግግር የከፈቱት የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትሩ ዶ/ር ሺፈራው ነበሩ፡፡ ሥልጠናው በክቡር ሚኒስትሩ ንግግር መከፈቱ ግን ከየክልሉ ተጠርተው ሥልጠናውን ከታደሙ ወደ 1500 የሚጠጉ ሙስሊሞች፣ ከ500 የማያንሱት አቋርጠው ከመውጣት አላገዳቸውም፡፡ በነገራችን ላይ፣ ከሐሮማያው ሥልጠና በኋላም፣ አዲስ አበባ ውስጥ በተካሄዱ የ‹አሕባሽ›አጥምቆት ጉባዔዎች ላይ ሚኒስትሩ ‹‹ውድ ጊዜያቸውን ሰውተው››የመክፈቻ ንግግር ከማድረጋቸውም በላይ ሥልጠናው ሲጠናቀቅም ለሠልጣኞች የምስክር ወረቀት ሰጥተዋል፡፡]

እርግጥ መንግሥት ‹‹በእነዚህ ሥልጠናዎች ላይ የምገኘው ለተሳታፊዎቹ በሕገ መንግሥቱ ዙርያ ግንዛቤ አስጨብጥ ዘንድ በጠቅላይ ምክር ቤቱ ስለተጠየቅሁ ነው››ሲል ነግሮናል፡፡ ለሐሮማያው ሥልጠና ከየክልሉ ከተጠሩት ሙስሊሞች መካከል 500 ያህሉ ‹‹ሥልጠናውን››አቋርጠው የወጡት፣ ‹‹ለምን ስለ ሕገ መንግሥት ግንዛቤ አስጨበጣችሁን?››ብለው ነውን? አይደለም፡፡ ውሎ ሳያድር ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ዳር እስከ ዳር ማጉረምረም የጀመሩትስ ‹‹ለምን ሕገ መንግሥቱ በሙስሊም ወንድሞቻችን ላይ እንዲሠርጽ ይደረጋል?››ብለው ነውን? አይደለም! መላው የአገሪቱ ሕዝብ ስለ ኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት ድንጋጌዎች ጠለቅ ያለ ግንዛቤ ቢጨብጥ፣ ሙስሊሞች ይደሰቱ እንደሁ እንጂ የሚያጉረመርሙበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ከሕዝቡ ግንዛቤ መጨበጥ የበለጠ ግን ሙስሊሞችን ጨምሮ መላው ኢትዮጵያውያን ከልብ የሚደሰቱት መንግሥት ሕገ መንግሥቱን አክብሮ ቢያስከብር ነበር፡፡ ካለፉት በርካታ ወራት ጀምሮ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ያለማቋረጥ እያጉረመረሙ ያሉትም ይህ ባለመሆኑ ነው መንግሥት ሕገ መንግሥቱን በመጣሱ!

መንግሥት ከ1950ዎቹ ወዲህ በሊባኖስ ምድር በተቋቋመ ‹‹አሶሴሽን ኦፍ ኢስላሚክ ቻሪቲስ››(AICP) የሚባል የበጎ አድራጎት ድርጅት አማካይነት እየተሰበከ የሚገኘውን የ‹‹አሕባሽ››አስተምህሮ ‹‹ነባሩ እስልምና››ብሎ በማንቆለጳጰስ፣ ‹አሕባሻዊው›ጠቅላይ ም/ቤት ሙስሊሙን ኅብረተሰብ በአሕባሽ አስተምህሮ ለማጥመቅ ለሚያካሂደው ዘመቻ በቀጥታም በሉት በተዘዋዋሪ ይሁንታውን ችሯል፡፡ በአንጻሩ መላው የኢትዮጵያ ሙስሊም ኅብረተሰብ ‹‹ሱፊዩም››ሆነ ‹‹ሰለፊዩ››ተቋማችን የ‹‹አህባሽ››አስተምህሮ ማስፋፊያ ሊደረግ አይገባም፡፡ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ የ‹‹አሕባሽ››ን አስተምህሮ የመቀበል፣ የመተግበር እና የማስተማር ሕገ መንግሥታዊ መብት አለው፡፡ ነገር ግን የእኛ ተቋም ለ‹‹አሕባሽ››አስተምህሮ አራማጆች ተላልፎ ሊሰጥ አይገባም፡፡ ፈጽሞ ያልመረጥናቸው የ‹‹አሕባሽ››አስተምህሮ አራማጆች ተቋማችንን ሊቆጣጠሩ፣ እምነታቸውንም በሰፊው ሙስሊም ሕዝብ ላይ ሊጭኑ አይችሉም፡፡ የመጅሊሳችንን መሪዎች የመምረጥ መብታችን ይከበር! እያሉ ‹‹ለመንግሥት ባልተመቸ››እጅግ ሰላማዊ መንገድ እየጮሁ ነው፡፡

ኢትዮጵያዊው ሙስሊም ለ‹‹ወዮልህ!››ዛቻ እና ማስፈራሪያ በርግጎ፣ ‹‹አክራሪ››እና ‹‹አሸባሪ››በሚሉ ቅጥያዎች ተሸማቆ ይህን ከመሠረታዊ የእምነቱ ጉዳይ ጋር የሚገናኝ ጥያቄ እርግፍ አድርጎ ይተዋል ተብሎ ይታሰባልን? ይህንን ጉዳይ አለቅጥ ለጥጦ በኢትዮጵያ ምድር ኢስላማዊ መንግሥት ከመመሥረት ጋር ማያያዝስ ምን ይጠቅማል? የትስ ያደርሳል? ይህንን የሙስሊሙ ሕዝብ ጥያቄ ተገቢነት ለመረዳት የግድ ሙስሊም መሆን አያስፈልግም፡፡ ‹‹እንዲህ ዓይነት ነገር በእኔ ላይ ቢፈፀም ኖሮ አሜን ብዬ እቀበላለሁኝን?››ብሎ ራስን መጠየቅ በቂ ነው፡፡

እስካሁን ከታየው ሁኔታ በመነሳት መንግሥት የሙስሊሙን ሕዝብ ጥያቄዎች ለማስተናገድ የመረጠው አካሄድ ለችግሩ እልባት የሚያስገኝ አይመስለኝም፡፡

በፕሮፓጋንዳው መስክ እየተሠራ ያለው ነገር ደግሞ እጅግ አሳፋሪ እና ፍፁም ኃላፊነት የጎደለው እንደሆነ በግልጽ እየታየ ነው፡፡ በአገር ውስጥም ሆነ በባህር ማዶ የሚኖሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በአንድ ድምጽ እየጮሁበት ያሉትን ግልጽ የሕዝብ ጥያቄ ‹‹የጥቂት ስውር ዓላማ ያላቸው ግለሰቦች››አድርጎ ለማጣጣል መሞከር ነገሮችን ያካርር እንደሁ እንጂ ከቶውንም አያለዝብም፡፡ መንግሥት በሚቆጣጠራቸው የህትመትና የኤሌክትሮኒክ ሚዲያዎች ላይ የሚሠሩ ጋዜጠኞች፣ ‹‹በዚህ እና በዚያ አቅጣጫ ፃፉ››ስለተባሉ ብቻ፣ ጠለቅ ብለው በማያውቁት፣ ሥራዬ ብለውም ባልተከታተሉት ጉዳይ ላይ ጨርተው ጨርተው እላቂያቸው የቀረ ውል የለሽ ቃላትን በመደረት ኃላፊነት በጎደለው ተግባር ላይ ባይተጉ መልካም ነው፡፡ መንግሥት የያዘው አቋም አደገኛ ይመስለኛል፡፡ ይህንን አደገኛ አቋም በማራገብ እና በመለጠጥ ነገሮችን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ መምራት ለአገራችን ሰላም አያመጣም፤ ልማትን አያፋጥንም፤ ዴሞክራሲን አያጎለብትም፡፡ የሕዝብን ድምጽ መስማት፣ ለሕዝብ ጥያቄም ተገቢውን ምላሽ መስጠት ነው የሚጠቅመው፡፡ ሕዝብን መናቅ ማንንም የትም አያደርስም፡፡

መነሻዬ ላይ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ካላበዱ በቀር በኢትዮጵያ ኢስላማዊ መንግሥት ስለመመሥረት ሊያስቡ አይችሉም ማለቴን ታወሰኝ፡፡ አሁን ጽሑፌን ልዘጋ ስል ደሞ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የማያደርጓቸው ሌሎች ሁለት ነጥቦች ትዝ አሉኝ፤ አንድያ ተቋማቸውን ‹‹አሕባሽ››ለሚባል መጤ አስተምህሮ አራማጆች አሳልፈው የሚሰጡ፣ የ‹አሕባሽ›ን አስተምህሮ በግድ እንጫንባችሁ ሲሏቸውም ‹በጄ›የሚሉ አይመስለኝም በእርግጥም ካላበዱ በስተቀር! እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች አላበዱም፡፡

Mega World NewsFacebook TwitterMyspaceFriendfeedTechnoratidel.icio.usDiggGoogleYahoo BuzzStumbleUponWeekend Joy

Share

Leave a Reply

  

  

  

You can use these HTML tags

<a href=""title=""><abbr title=""><acronym title=""><b><blockquote cite=""><cite><code><del datetime=""><em><i><q cite=""><strike><strong>